የየመን ተዋጊ ሀይሎች እስረኞችን ለመለዋወጥ ውይይት ላይ ናቸው።
የየመን ተዋጊ ሀይሎች እስረኞችን ለመለዋወጥ ውይይት ላይ ናቸው
ሁለቱ ወገኖች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አነሳሽነት ኦማን ላይ በሚወያዩበት ወቅት በሁለቱም በኩል የመግባባት መንፈስ ታይቷል ተብሏል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ሁለቱ ተዋጊ ሀይሎች በሁዴይዳ ወደብ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ ካደረገ በኋላ ሳይውል ሳያድር ስምምነቱ ቢጣስም አሁንም የሰላም ስምምነቱ እንዲከበር እና እስረኞችን እንዲለዋወጡ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሁቲዎች እና በሳውዲና አጋሮቿ የተቋቋመው የየመን መንግስት ባለፈው ታህሳስ ወር የ15 ሺህ እስረኞችን ስም ዝርዝር የተለዋወጡ ሲሆን ይህን ዶክመንት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ቀይ መስቀል ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከመንግስት በኩል የተወከሉትን ልኡካን የሚመሩት ሀዲ ሀይግ በጥሩ መንፈስ እየተወያየን ነው፤ ቀደም ሲል የተስተዋሉ ክፍተቶችም በአሁኑ ውይይት እየተፈተሹ ነው ብለዋል፡፡
ሁቲዎችን ወክለው የተገኙት ቃድር ሙርታዳ በበኩላቸው ያልተቋጩ ጉዳዮችን ዳር ለማድረስ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ በሁለቱም ወገኖች በኩል ስምምነት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡
በሁዴይዳ ወደብ ያለው የሰላም ሁኔታ በአሁኑ ወቅት እንዲስተካከልና በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎቸ የእርዳታ ቁሳቁሶች እንዲገቡላቸው ሁለቱም ወገኖች በጋራ መስራት እንዳለባቸው የመንግስታቱ ድርጅት አሳስቧል፡፡