የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በኢምሬት ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚዎች ምክንያት ጋብ ብሎ የነበረው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬና እና ነገ ይከናወናሉ፡፡
ዛሬ ምሽት ስድስት ያህል ጨዋታዎች ሲደረጉ ምሽት 4፡45 ኤምሬትስ ላይ የኡናይ ኢምሪው አርሰናል ካርዲፍን ያስተናግዳል፤ ክራቨን ኮቴጅ ላይ የክላውዲዮ ራኔሪው ፉልሃም ብራይተንን ይገጥማል፡፡
ግርጌ ላይ የተቀመጠው ሀደርስፊልድ በጆን ስሚዝ ኢቨርተንን ያስተናዳል፡፡ የኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶው ወልቭስ ከመዶሻዎቹ ዌስት ሃም ዩናይትድ ጋር ይፋጠጣሉ፡፡
ምሽት 5፡00 ላይ በሶልሻዬር እየተመራ ጥሩ ግስጋሴ ላይ ያለው ማንችስተር ዩናይትድ በኦልትራፎርድ በርንሊን እንዲሁም በተመሳሳይ ማግቢሶቹ ኒውካስትል ዩናይትድ ሴንት ጀምስ ፓርክ ላይ ከፔፕ ጓርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ጋር ይጫወታሉ፡፡
የሳምንቱ መርሀግብር በነገው ዕለት ሲቀጥል፤ ምሽት 4፡45 ላይ የማውሪዚዮ ሳሪውን ቼልሲ ወደ ዲን ኮርት አቅንቶ በርንማውዝን ሲጎበኝ የለንደኑ ክሪስታል ፓላስ ወደ ደቡብ ጠረፍ አምርቶ ሳውዛምፕተንን ሴንት ሜሪ ላይ ይፈትናል፡፡
5፡00 ላይ ደግሞ በአንፊልድ ሮድ በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ አናት ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ሌስተር ሲቲን ያስተናግዳል፡፡
በኤፍ ኤ ካፕ እና ሊግ ካፕ ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ቶተንሃም ዊምብሌ ላይ ወደ ድል ጎዳና ለመመለስ እያለመ ዋትፎርድን ይገጥማል፡፡
ሊጉን ሊቨርፑል በ60 ነጥብ ይመራል ፤ ማ.ሲቲ በ56 ሁለተኛ፤ ቶተንሀም በ51 ሶስተኛ፤ ቼልሲ በ47 ነጥብ አራተኛ እንዲሁም አርሰናል እና ማ.ዩናይትድ በ44 ነጥብ አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ካርዲፍ፣ ፉልሃምና ሀደርስፊልድ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡