የአዲስ አበባ ውሃ አልተበከለም አለ የከተማው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን
አርትስ 08/01/2011
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ለአርትስ ቲቪ እንደተናገሩት ከትናንት ጀምሮ የአዲስ አበባ ውሃ በመርዝ ተበክሏል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው ወሬ ፍጹም ሃሰት ነው።
ባለስልጣኑ በየዕለቱ ከግድብ ጀምሮ እስከማጣሪያ ጣቢያዎችና ተጠቃሚዎች ድረስ የሚደርሰውን ውሃ በአለምአቀፉ ጤና ድርጅት በተመሰከረለት ላቦራቶሪና ኬሚካል ፍተሻ እንደሚያደርግ አቶ እስጢፋኖስ ጠቁመዋል።
ካለፈው እሁድ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በከተማው ጥቅም ላይ እየዋለ ባለው የመጠጥ ውሃ ላይ የተለመደው ፍተሻና ማጣራት ሲደረግ እንደነበር የተናገሩት አቶ እስጢፋኖስ በውጤቱ አንዳችም የውሃ መበከል ችግር እንዳልታየ ገልጸዋል።
እንዲህ ያሉ የሃሰት ወሬዎች ሆን ብለው ህዝቡ እንዲረበሽ ከሚፈልጉ እኩይ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች የሚነዙ መሆናቸውን የገለጹት አቶ እስጢፋኖስ ህብረተሰቡ በዚህ ሳይረበሽ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴውን መቀጠል ይችላል ብለዋል።
አጠራጣሪ ነገር አግኝቻለሁ የሚል አካል ካለ በየአካባቢው በሚገኙት የባለስልጣኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ማሳወቅ እንደሚችልም አቶ እስጢፋኖስ ተናግረዋል።