የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ ማገዝን ዓላማ ያደረገ ዓለም አቀፍ የልማት ፈንድ ተመሠረተ፡፡
የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ ማገዝን ዓላማ ያደረገ ዓለም አቀፍ የልማት ፈንድ
ተመሠረተ፡፡
ፈንድ የተመሰረተዉ በሰሜን አሜሪካ ነዉ፡፡
ፈንዱ በአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጡትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ዓላማ ያደረገ መሁኑን የባለአደራ ቦርዱ ሰብሳቢ ዶክተር ሶስና ንጉሴ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ዶክተር ሶስና ፈንዱ በኢኮኖሚው ዘርፍ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የልማት ፈንዱ የአጭር እና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በመንደፍ መቋቋሙንም ነው ያስታወቁት፡፡ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና፣ የመማሪያ ክፍሎች እና መጠለያ ችግሮችን ለማቃለል መታሰቡም በመግለጫቸው ተመላክቷል፡፡
ጥናቶችን በመስራት እና ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ውጤታማ ለማድረግ መታቀዱንም ዶክተር ሶስና አስታውቀዋል፡፡ ፈንዱ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን እና ወዳጆችን በማስተባበር የአማራን ህዝብ ችግሮች ለመቅረፍም ሰራል፡፡
ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የአማራ ምሁራንን እና ባለሃብቶችንም ያሳትፋል፡፡
የአማራ ዓለም አቀፍ የልማት ፈንድ ወደፊት የተለያዩ መዋቅሮችን እንደሚያደራጅና አሁን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሰባት አባላት ባሉት የቦርድ አመራሮች መመስረቱንም ሰምተናል፡፡