የመኪና ቀበኞችን በቁጥጥር አውያለሁ-የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን::
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 21 የመኪና ቀበኞችን በቁጥጥር አውያለሁ-የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን:: የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተሸከርካሪ ስርቆት ተሰማርተው የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ አለ፡፡ በቡድን በመደራጀት እንዲሁም በተናጠል ተሽከርካሪዎችን ሲሰርቁ እና ሲተባበሩ የነበሩ 21
ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡ ቀደም ሲል ፈፃሚያቸው ያልታወቀ በሚል የተመዘገቡ የሥርቆት ወንጀሎች በእነዚህ ተጠርጣሪዎች እንደተፈፀሙ በማረጋገጥ የተሰረቁትን ተሽከርካሪዎች ማስመለሱንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገ ምርመራ 9 ተሽከርካሪዎችን መስረቃቸውን በማረጋገጥና ከያሉበት በማስመለስ በ10 መዝገቦች ምርመራ እየተጣራባቸው ነው ተብሏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከሚኒባስ እስከ ካቻማሊ የህዝብ ማመላለሻ እና ሲኖትራክ የጭነት መኪኖችን መስረቃቸውን ፖሊስ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡ ከተሰረቁት ተሸከርካሪዎች መካከል የውስጥ አካላቸው ተፈታትቶ ከተሸጠ በኋላ በምሪት ከተሸጡበት የተመለሱም ይገኙበታል፡፡
ወንጀሉን ለመፈፀም ለራሳቸውና ለተያዥ ሃሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በጥበቃ ስራ የሚቀጠሩ ግለሰቦች መኖራቸውን እዲሁም የጋራዥ ሰራተኛ ሆነው የደንበኛቸውን የመኪና ቁልፍ አስቀርፀው ለወንጀል ፈፃሚዎች የሚሰጡ ግለሰቦች ማጋጠማቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡