ኪም ጆንግ ኡን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለማዉራት ቬቴናም ገቡ፡፡
ኪም ጆንግ ኡን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለማዉራት ቬቴናም ገቡ፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካው ፕሬዜዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለሚያደርጉት ውይይት ቬቴናም ገቡ፡፡
ባለፈው አመት ሲንጋፖር ላይ ከተካሄደው ታሪካዊውና የመጀመሪያው ዙር ጉባኤ የቀጠለ ነው የተባለለት የሁለቱ ሀገራት ውይይት ቬትናም ላይ ይካሄዳል፡፡
ኪም ጆነግ ኡን በቅንጡ ባቡራቸው አራት ሺህ ኪሎ ሜትር ተጉዘው ዶንግ ዳንግ ድንበር ሲደርሱ በቀይ ምንጣፍ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ቀጥሎም ወደ ዋና ከተማዋ ሃኖይ በከፍተኛ ጥበቃ ታጅበው እና በደጋፊዎች ጩኸት እና ጭብጨባ ተከበው ሄደዋል፡፡
ኪም ልክ እንደ አምናው ሁሉ በዚህኛው ጉዞአቸው ያካተቱት እህታቸውን ኪም ዮጆነግ እና የቀድሞው ጄኔራል ኪም ዮንግ ቾል መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዋይት ሃውስ ቃል አቀባዩዋ ሳራ ሳንደርስ ገለጻ ፕሬዜዳንት ትራምፕ እና ኪም ረቡዕ ምሽት ላይ የአንድ ለአንድ ውይይት ካደረጉ በኋላ አማካሪዎቻቸው በተገኙበት የእራት ፕሮግራም ይኖራቸዋል፡፡
በቀጣዩ ቀን ደግሞ መሪዎቹ በወሳኝ እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባለፈው አመት በሲንጋፖር በተደረገው ጉባኤ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን ወደ ስራ ለማዋል የሚያስችሉ ውሳኔዎች ከዘንድሮው ጉባኤ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በሲንጋፖሩ ጉባኤ መሪዎቹ የኒውኩለር ጣቢያዎችን የማምከን ሂደቱንና አተገባበሩን አስመልክቶ ግልጽ ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ጉባኤውን ተከትሎ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በዲፕሎማሲ ረገድ መሻሻሎች መታየታቸው ተነግሯል፡፡