እንግሊዝ ራስ ማጥፋትን ተከላካይ ሚኒስቴር አቋቋመች
አርትስ 01/02/2011
እንግሊዝ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ነፍስን በገዛ እጅ የማጥፋት ጉዳይ ለመቀነስ በሚኒስቴር ደረጃ ራስን የማጥፋት ተከላካይ ሚኒስትር (suicide prevention Minister) መሾሟ ተሰምቷል።
ይህ ሹመት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ለነበሩት ጃኪ ፕራይስ ነው የተሰጠው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ይህን ሹመት የሰጡት የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን በተከበረበት በትናንትናው ዕለት ነው።
የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ትናንት በለንደን ከ50 አገራት የመጡ የጤና ሚኒስትሮች በተገኙበት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በዕለቱ የቀረበው ጥናት በእንግሊዝ በዓመት በአማካይ 4500 ዜጎች እራሳቸውን እንደሚያጠፉ ጠቁሟል።
እንግሊዝ ውስጥ በዚህ ዙሪያ በተደረገ ጥናት የአእምሮ ጤና ችግር ያጋጠማቸው ዜጎች በዘርፉ የሰለጠነን ሐኪም ለመጎብኘት እስከ ሦስት ወራት ለመጠበቅ እንደሚገደዱ እና በርካታ ዜጎችም ራስን ለማጥፋት እንደ አንድ ምልክት በሚታዩት የድብርትና ጭንቀት በሽታዎች እየተሰቃዩ እንደሆነ ተነግሯል።
ከዚህ ቀደምም ሀገሪቷ የሳቅ ሚኒስቴር እና ብቸኝነትን የማስወገድ ሚኒስቴር አቋቁማ ነበር፡፡