በየመን የአልቃይዳ መሪ ካሊድ ባታርፊ በቁጥጥር ስር ውሏል ተባለ::
አዲስ አበባ፣ጥር 28፣ 2013 በየመን የአልቃይዳ መሪ ካሊድ ባታርፊ በቁጥጥር ስር ውሏል ተባለ:: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየመን የአልቃይዳ መሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታወቀ፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት የክትትል ቡድን ትናንት ሃሙስ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ካሊድ ባታርፊ በቁጥጥር ስር ከዋለ መቆየቱን ጠቁሟል፡፡
በየመን የአልቃይዳ መሪዉ ባታርፊ በፈረንጆቹ 2020 መጀመሪያ አመታ ላይ ነበር የሽብር ቡድኑን እንዲመራ የተመረጠው እንደ አረብ ኒውስ ዘገባ፡፡
ምክትሉ ሰዓድ አቲፍ አል-አውላቂ አል ማህራህ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ጋይዳ ከተማ ተካሂዶ በነበረው ዘመቻ መገደሉንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በኦሳማ ቢን ላደን እና አጋሮቹ መመስረቱ የሚነገርለት አልቃይዳ የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በአሜሪካ እና በሌሎችም ሃገራት በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወስ ነው፡፡ ቢንላደን አሜሪካ በባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን ባካሄደችው ዘመቻ በፓኪስታን
አቦታባድ መገደሉም አይዘነጋም፡፡