በኤፍ. ኤ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ማንችስተር ሲቲ ከ ብራይተን ጋር ተገናኝቷል
የኤምሬትስ ኤፍ. ኤ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነዋል፡፡
ቅዳሜ ሶስት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ ማንችስተር ሲቲ ወደ ዌልስ ምድር አምርቶ ስዋንሲን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን ተዋህዷል፡፡ ሲቲ ከ2 ለ 0 መመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ ያደረጉ ግቦችን፤ ሰርጂዮ አጉዌሮ እና ቤርናርዶ ሲልቫ ሲያስቆጥሩ የስዋንሲው ግብ ጠባቂ ኖርድፌልት በራሱ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡
ሌላኛው የማንችስተር ከተማ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ሞሊኒክስ ተጉዞ በወልቭስ 2 ለ 1 ተረትቶ ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ ራኡል ኽሜኔዝ እና ዲዮጎ ጆታ ለተኩላዎቹ ሲያስቆጥሩ ማርከስ ራሽፈርድ ለዩናይትድ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ አገናኝቷል፡፡
ዋትፎርድ ቪካሬጅ ላይ በካፑ እና አንድሬ ግሬይ ግቦች ክሪስታል ፓላስን 2 ለ 1 አሸንፎ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለ ቡድን ሁኗል፡፡
ትናንት ደግሞ የፕሪምየር ሊጉ ቡድን ብራይተን ከሜዳው ውጭ ከሚልዌል ጋር ተገናኝቶ ሙሉ ጨዋታውን በ2 ለ 2 አቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ በተሰጠው የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ብራይተን 5 ለ 4 አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሻግሯል፡፡
በግማሽ ፍፃሜው የዕጣ ድልድል ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን ከማንችስተር ሲቲ ሲገናኝ፤ ወልቨርሃምፕተን ዋንደረርስ ደግሞ ከዋትፎርድ የሚጫወት ይሆናል፡፡
የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ ከሶስት ሳምንታት በኋላ በዌምብሌይ ስታዲየም ይከናወናሉ፡፡