በሶሪያ ህፃናት ላይ ሰው ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮም ፊቷን አዙራባቸዋለች
በሶሪያ ህፃናት ላይ ሰው ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮም ፊቷን አዙራባቸዋለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የህጻናት መርጃ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በርስ በርስ ጦርነት በደቀቀችው ሶሪያ በተከሰተው ከባድ ቅዝቃዜ ሳቢያ 15 ስደተኛ ህፃናት ሞተዋል፡፡
ህፃናቱ ህይወታቸው ለማለፉ በሀገሪቱ ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት የተከሰተው የምግብ እና የህክምና እጦትም ትልቅ ድርሻ አለው ተብሏል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው ከሞቱት ህፃናት መካከል አስራ ሶስቱ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ሲሆኑ ሶሪያ ከጆርዳን ጋር በምትዋሰንበት የአል ራክባን የስደተኞች ጣቢያ ህይወታቸው ያለፈው፡፡
የአካባቢው የዩኒሴፍ ዳይሬክተር ጊርት ካፕሌር በአል ራክባን የስደተኞች ጣቢያ ከባዱ ቅዝቃዜ እና ጎስቋላ አኗኗር ተዳምረው የህጻናቱን ህይወት አደጋ ላይ ጥለውታል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዚህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ 50 ሺህ የሚሆኑ ስድተኞች በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት እንደሚያሳየው በሶሪያ በተቀሰቀሰው የርስ በርስ ጦርነት 10 ሺህ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
በጦርነቱ ሳቢያ መተላለፊያ መስመሮች በመዘጋታቸው ህፃናት በቀላሉ ታክሞ በሚድን በሽታ ህይወታቸው ሲቀጠፍ ማየት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይቅር ያማያስብል ሰው ሰራሽ ጥፋት ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡