መኢአድ አንቀጽ 39 እንዲሰረዝ ጠየቀ::
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አገር ለማፍረስ የተቀመጠ ነው ያለውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 እንዲሰረዝ ጥያቄ አቀረበ፡፡
ፓርቲውን ይህን ጥያቄ በይፋ ያቀረበው ሐሙስ ነሐሴ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ‹‹አገር ለማፍረስ የተቀመጠው አንቀጽ 39 የወለደው ችግር የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፤›› በማለት፣ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት መሆኑን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
ለ27 ዓመታት የተገነባው የጥላቻ ግንብ ዘርና ቋንቋን መሠረት በማድረግ የተመሠረተው የፌዴራሊዝም ሥርዓት፣ ውጤቱ እንደዚህ ሕዝብን በማጋጨት የአገርን ንብረት በማውደም ላይ ይገኛል ሲሉ መኢአድ ሥጋቱን ገልጿል፡፡
መኢአድ ይህን ያለው ሰሞኑን በጂግጂጋ ከተማ የደረሰውን ግጭት መሠረት አድረጎ ሲሆን፣ በአንቀጽ 39 ሳቢያ እንዲህ ያሉ የአገርን አንድነትና ክብር የሚነኩ ጉዳዮች እንደሚከሰቱ በማስጠንቀቅ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሥጋቱን ሲገልጽ መቆየቱንም አስታውቋል፡፡
‹‹ዛሬ ወደ ሶማሌ ክልል በመሄድ አገራቸውንና ወገናቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ዜጎች ሕገወጥ በሆኑ ግለሰቦች በዘራቸው የተነሳ ብቻ እንዲገደሉ ተፈርዶባቸዋል፣ ተሰደዋል፣ ተጠቅተዋል፣ ንብረታቸውም እንዲወድም ተደርጓል፡፡ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ደግሞ ቤተ እምነቶች እንዲቃጠሉ ተደርጓል፤›› በማለት፣ የብሔር ፌዴራሊዚሙ ያመጣው ችግር ሳይባባስ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
‹‹አሁን በየቦታው እየተፈጸመ ያለው በዘር ላይ የተመሠረተ ግጭት ወደ ከፋ ደረጃ በመሸጋገር ላይ ስለሆነ፣ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ድርጅታችን ይጠይቃል፤›› ብሏል፡፡
‹‹በዚህም መሠረት መንግሥት በአስቸኳይ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ሲልም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡