የኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦች የምርመራው ውጤት በምንፈልገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም አሉ፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ መኪናቸው ውስጥ ባልታወቀ ምክንያት ህይወታቸው አልፎ ከተገኘ ሁለት ሳምንታት አለፉ።
ቢቢሲ እንደዘገበዉ የኢንጂነር ስመኘው ባለቤት የወ/ሮ ዕሙን ጌታሁን ታናሽ ወንድም የሆነው አካሉ ጌታሁን ”ሃዘናችን እጅግ ከባድ ቢሆንም እየበረታን ነው። ከቀብሩ ጀምሮ መንግሥት እየደገፈን ነው። ምንም ያወጣነው ወጪ የለም” ብሏል።
አካሉ ጨምሮም “የስመኘው የመጀመሪያ ልጅ የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስዶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲመደብ እየተባበሩን ነው” በማለት ከመንግሥት የተደረገላቸውን ድጋፍ የገለጸ ሲሆን ”ገዳዩን ለፍርድ ለማቅረብ ግን ፖሊስ በምንፈልገው ፍጥነት እየሄደልን አይደለም” ሲል በምረመራው ውጤት መዘግየት ቤተሰቡ ቅር እንደተሰኘ ተናግሯል፡፡።