በፀጥታ ችግር ሳቢያ ንብረታቸውን ላጡ አሰሪዎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 በፀጥታ ችግር ሳቢያ ንብረታቸውን ላጡ አሰሪዎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ :: የድጋፍ ማሰባሰቢያው ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት ለዓመታት ሰርተው ያፈሩት ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸውን አሰሪዎች መልሶ ሟቋቋሚያ ነው ተብሏል።”አሰሪው ለአሰሪው” የተሰኘው ይህ መርሃ ግብር የአገሪቷን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ለመፍጠርና ስራ ፈጣሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
የመርሃ ግብሩ ግብ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት በገንዘብና በአይነት በማሰባሰብ ለተጎጂዎቹ በፍትሀዊነት በማከፋፈል ወደ ስራ መመለስና ተነሳሽነታቸውን ማነቃቃት እንደሆነም ተገልጿል።የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተፈጠረው ችግር የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በሆኑት አሰሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ጉዳት የደረሰባቸውን አሰሪዎች መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋነኛው መፍትሄ የሕግ የበላይነትን ማስከበር በመሆኑ መንግስት በዚህ ላይ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።