የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚጠቅሙ ተብሎ በጤና ባለሙያዎች የተለዩ ምግቦች እንደሌሉ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ::
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚጠቅሙ ተብሎ በጤና ባለሙያዎች የተለዩ ምግቦች እንደሌሉ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ::
የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ከበሽታው የሚያድኑ ተብሎ እስካሁን በጤና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ተመሥርተው የቀረቡ የተለዩ የምግብ ዓይነቶች አለመኖራቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ገለጹ።ኅብረተሰቡ አሁንም በመንግሥትና በጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡለትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ከቫይረሱ ራሱንና ወገኑን መከላከል እንደሚገባው ጠቁመዋል።ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እስካሁን የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ከበሽታው ለማዳን ‘ይህ ምግብ ይሆናል’ የሚል ምንም አይነት የተረጋገጠ ነገር የለም።ያም ሆኖ ኅብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ ጤናን ለመጠበቅ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና ማዘውተር እንዲሚገባው አስገነዝበዋል።”ኅብረተሰቡ በሚመገባቸው ምግቦች ሳይዘናጋ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ሳያስተጓጉል አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል።አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሊያ፤ ኅብረተሰቡ እስካሁን የሚያደርጋቸውን የመከላከያ ተግባራት ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል።በኅብረተሰቡ ዘንድ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አጠቃቀም ላይ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸው፤ በዚህ ላይ አካላዊ ርቀትን መጠበቅን በማከል ቫይረሱን መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።