የ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ
የፕሪምየር ሊጉ የ19ኛ ሳምንት መርሐግብር በዛሬው ዕለት በሚደረግ አንድ ጨዋታ ሲጀመር፤ ብቸኛው ግጥሚያ 9፡00 ሰዓት ሲል ደቡብ ፖሊስ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ይጫወታል፡፡
ቅዳሜም አንድ ጨዋታ ሲካሄድ፤ ባህር ዳር ከነማ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ተጉዞ በ9፡ 00 ሰዓት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይፋለማል፡፡
በዕለተ ዕሁድ ክልል ስታዲየሞች ላይ አራት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ በተመሳሳይ 9፡00 ሰዓት ይደረጋሉ፡፡
አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ደግሞ አንድ ጨዋታ ቀን 10፡00 ሰዓት ላይ ሲደረግ፤ ላለመውረድ እየተፍጨረጨሩ የሚገኙት መከላከያ እና ደደቢት ይገናኛሉ፡፡
ድሬዳዋ ከነማ ድሬዳዋ ላይ ጅማ አባጅፋርን ያስተናግዳል፡፡ የሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ በትግራይ ስታዲየም ከወላይታ ድቻ ይጫወታል፡፡
ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡
አስቸጋሪ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ትግራይ ክልል አምርቶ ሽረ ላይ ከስሑል ሽረ ከባድ ጨዋታ ያደርጋል፡፡
የሳምንቱ መርሀግብር መቋጫ ፍልሚያ አዲስ አባባ ስታዲየም ሰኞ 11፡00 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ መካከል ይከናወናል፡፡
ጨዋታው በሳምንቱ በተሻለ ተጠባቂ ሲሆን አርቢትር ባምላክ ተሰማ ይመሩታል፡፡