loading
በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ በቂ አለመሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ በቂ አለመሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ ምእራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቅለው በጊዜያዊ በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙትን የአማራ እና የቅማንት ተፈናቃዮችን ጎብኝቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ሁለቱን የመጠለያ ጣቢያዎች በጎበኘበት ወቅት በምዕራብ ጎንደር ዞን አይንባ ቀበሌ ሰፍረው የሚገኙት የተፈናቃዮች ብዛት 11ሺህ 388 ሲሆን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንቸው ቀበሌ መጠለያ ጣቢያ የሰፈሩት ደግሞ ቁጥራቸው 6ሺህ 785 መሆኑን አረጋግጧል፡፡
በተመሳሳይም ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአደጋ መከላከል፣ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች በተገኘው መረጃ በማዕከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች የተፈናቃዮች ብዛት 57ሺህ 175 እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡
ለተፈናቃዮች የሚደረገው የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ በቂ አለመሆኑን፣ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎችም ደህንነታቸው መሉ በሙሉ የተጠበቀ ነው ማለት እንዳማይቻል ቋሚ ኮሚቴው ተረድቷል፡፡
መጠለያ ጣቢያዎች ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ለነፍሰ ጡር እናቶች እና ለህጻናት ስቃዩ የከፋ እንደሆነ፣የምግብና የውሀ አቅርቦት፣ የመኝታ፣ የመጸዳጃ ቤት እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ቋሚ ኮሚቴው መገንዘብ የቻለ ሲሆን ተፈናቃይ የሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መታገድ አግባብነት እንደሌለው አመልክቷል፡፡
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው የሰፈሩባቸው መጠለያ ጣቢያዎች የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ገልጸው የሚደረግላቸው የእርዳታ እህል፣ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ለባሰ ስቃይና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ ብሶታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከመንግስት የሚጠብቁት ከጊዜያዊ እርዳታ ባለፈ ቀድሞ ወደነበሩበት ቦታ ወስዶ በዘላቂነት ሊያቋቁማቸው እንደሚገባ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአማራ እና በቅማንት ህዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን በሚሰሩ ሀይሎች ላይም መንግስት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ማስከበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በሁለቱ ህዝቦች መካከል የማያግባቡ ጉዳዮችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍትህአዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንግድ ተፈተው በሰላም አብሮ የመኖር ህሉናቸው መረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ መንግስት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት  ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰብ እያደረገ እንደሆነ እና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት እና አለመግባባት ፍትህአዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ምንጭ ተወካዮች ምክርቤት

 

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *