በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አበባ ክለቦች ሽንፈት አስተናግደዋል
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር 16ኛ ሳምንት መርሀግብር ጨዋታዎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል፡፡
በርካታ ግጥሚያዎች በክልል ስታዲየሞች ሲደረጉ፤ በሳምንቱ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ብቸኛ ግጥሚያ፤ መከላከያ መሻሻል እያሳየ ባለው ደቡብ ፖሊስ የ2 ለ 0 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡
ባህር ዳር ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በባለሜዳው ባህር ዳር ከነማ የ1 ለ 0 ሽንፈት ሲያስተናግድ፤ ሌላኛው የሸገር ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ አቅንቶ በድሬዳዋ ከነማ የተመሳሳይ 1 ለ 0 ሽንፈት ቀምሷል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ፋሲለደስ ላይ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 ረትቶ፤ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል፡፡
ትግራይ ላይ ደደቢት በተቀናቃኙ መቐለ 70 እንደርታ የ4 ለ 1 ሰፊ ውጤት ተረትቷል፡፡ መቐለም የሊጉን መሪነት ማጠናከር ችሏል፡፡
ወላይታ ድቻ ሶዶ ላይ ከስሑል ሽረ ጋር በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
በጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ መካከል የተካሄደው ግጥሚያ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ቅዳሜ እለት በተካሄደው ብቸኛ ግጥሚያ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፤ ሀዋሳ ከተማን 1 ለ 0 ድል አድርጓል፡፡
የሊጉን የደረጃ ሰንጠራዥ መቐለ በ38 ነጥብ ሲመራ፤ ሲዳማ በ30 ይከተላል፣ ፋሲል በ28 3ኛ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡