በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር ሲቲ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል፡፡
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር ሲቲ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል፡፡
ትናንት ምሽት የቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ፤ ወደ ቬልቲንስ አሬና ያመራው ማ.ሲቲ ከመምራት መመራት፤ ከመመራት ደግሞ አሸንፎ ወጥቷል፡፡
ሲቲዎች በሰርጂዮ አጉዌሮ ግብ ቀዳሚ ቢሆኑም ሻልከ የቫር ውሳኔን ባገኙ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች ታግዞ መምራት ጀመረ፤ ጎሎችን ደግሞ ናቢል ቤንታሊብ አስቆጥሯል፡፡ ይባስ ብሎ የሲቲው ተከላካይ ኦታሜንዲ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናበተ፡፡ የፔፕ ቡድን በቃ ተሸነፈ ሲባል መደበኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሊሮይ ሳኔ በቀድሞ ክለቡ ላይ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አደረገ፤ ራሂም ስተርሊንግ ደግሞ 90ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያዋን ጎል ከመረብ አገናኝቶ፤ ውሃ ሰማያዊዎቹ ባለድል ሆኑ፡፡
በዚህም የፔፕ ጓርዲዮላው ቡድን ለመልሱ ጨዋታ አጋዥ የሆነ ውጤት አሳክቷል፡፡
ሌላኛው ግጥሚያ ደግሞ ማድሪድ ላይ በተሰየመው ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ዩቬንቱስን ያስተናገደው አትሌቲኮ ማድሪድ 2 ለ 0 በመርታት በጣም አስፈላጊ ውጤት አግኝቷል፡፡
በቫር ውሳኔዎች በታጀበው የምሽቱ ጨዋታ አትሌቲ በአልቫሮ ሞራታ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም የቫር ውሳኔ ሽሮታል፡፡ ለስፔኑ ቡድን ዩራጓያዊው ሆሴ ማርያ ኸሜኔዝ እና አምበሉ ዲዬጎ ጎዲን አስቆጥረዋል፡፡ አሮጊቷ ሽንፈት ማስተናገዷን ተከትሎ ከሶስት ሳምንት በኋላ በሜዳዋ አሊያንዝ ስታዲየም ላይ ለምታደርገው የመልስ ፍልሚያ አሸንፋ ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡
በምሽቱ ግጥሚ የቫር ውሳኔዎች፣ የሮናልዶና የአትሌቲ ደጋፊዎች ብሽሽቅ፣ የአሰልጣኝ ዲየጎ ሶሞኔ የደስታ አገላለፅ እንዲሁም የተጫዋቾች ስሜታዊ መሆን ዋነኛ ትኩረቶች ነበሩ፡፡
በ16ቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ የመልስ ግጥሚያዎች ከ12 ቀናት በኋላ ጀምረው ይከናወናሉ፡፡