በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ስም ትምህርት ቤት ሊገነባ ነዉ፡፡
አርትስ 21/01/2011
በቡታጅራ ከተማ በሚገነባዉ ት/ቤት 95 በመቶ የሚሆኑትን ተማሪዎች በነፃ ተቀብሎ ያስተምራል።
ትናንት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ስም ሊገነባ መሆኑን ይፋ ካደረጉት አስተባባሪዎች መካከል የገቢ ማሰባሰብ ስራውን የሚመራው አቶ ብሩክ ዳንኤል እንደገለፀው፤ ግንባታው በጎ ፍቃደኛ በሆኑት ባለሀብት አቶ አህመድ ሁሴን ሃሳብ ጠንሳሽነት የሚጀመር ነው።
ትምህርት ቤቱን ለመገንባት 10 ሚሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል በባለሀብቱ የተመደበ ሲሆን ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ 120 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
የፕሮጀክቱ ጠንሳሽ እና ባለቤት የሆኑት አቶ አህመድ ሁሴን ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ እውቀትን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ከማስጨበጡ ባሻገር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ አኩሪ ባህል፣ ሰላም እና አንድነት ሁሉንም ዜጎች ያለምንም ልዩነት ያስተምራል። የትምህርት ቤቱ ዋና ዓላማም ኢትዮጵያዊነትን በአዲሱ ትውልድ ማስረፅ መሆኑን ለየኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል።