ኢሕአፓ ከ40 አመታት በላይ የውጪ አገር ቆይታ በኋላ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገባ
አርትስ 12/01/2011
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ከ40 አመታት በላይ የውጪ አገር ቆይታ በኋላ ዛሬ አዲስ አበባ ገባ።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ በላይነህ ንጋቱ፣ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም፣ አቶ መሃመድ ጀሚል እና ኢንጂነር ሰለሞን ገብረስላሴን የያዘ ከፍተኛ አመራር አባላት ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ተቀብለዋቸዋል።
ሊቀመንበሩ አቶ በላይነህ ንጋቱ እንዳሉት፤ ፓርቲው በአገሪቱ አሁን የተጀመረውን ለውጥ መሰረት እንዲይዝ የሚችለውን ያደርጋል።
በተፈጠረው እድል ህጋዊ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ፓርቲው ዝግጁ መሆኑን የገለፁት ሊቀመንበሩ ከአሁኑ የለውጥ አመራር ጎን በመሆን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በትጋት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣትም ከቀድሞ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ከወጣቱ ጋር የጋራ ምክክር እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
የፓርቲው ቃል አቀባይ ኢንጂነር ሰለሞን ገብረስላሴ በበኩላቸው በለውጡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ነገር ግን ለውጡን ለማደናቀፍ የሚታዩ እንቅስቃሴዎች ሊቀረፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመፍታትም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዴሞክራሲ የበለጠ እንዲሰፋ ፓርቲያቸው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የፓርቲው አመራሮች ከቦሌ አየር ማረፊያ ተነስተው ወደ ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም እያቀኑ ሲሆን በዚያም የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥና ሻማ የማብራት ስርዓት ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢህአፓ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻና አሻራ ያለው መሆኑ ይታወቃል።
በ1966 ዓም በኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ ኢህአፓ የህዝብን ጥያቄ በማንገብና ህዝባዊ እንቢተኝነትን በመምራትና በማስተባበር በአገሪቱ የንጉሳውያን አገዛዝ እንዲያበቃና የ’መሬት ላራሹ’ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል መሰረት ጥሏል።
የንጉሳዊ ስርዓቱን መውደቅ ተከትሎ ስልጣኑን ወታደራዊው ኃይል በመቆጣጠሩ ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት ጽኑ ፍላጎት የነበረው ኢህአፓ ስልጣን ከያዘው ኃይል ጋር በመላተሙ በርካታ አባላቱን በሞትና በእስር አጥቷል።
ከደርግ ማሳደድ አምልጠው ከአገር መውጣት የቻሉ አባላቱ በውጭ አገር በስደት ለረጅም አመታት ቆይተው ዛሬ ለመመለስ ችለዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ