የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ነገ ወደ አሜሪካ ይሄዳሉ
“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩንም እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የሚያደርጉት ጉዞ በአጠቃላይ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፥ በሀገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆነው ለሀገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያለመ ነው ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሎስ አንጀለስ እና በዋሽንግተን ዲ ሲ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ሐምሌ 24 ቀን ድረስ ነው በአሜሪካ ቆይታ የሚያደርጉት።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን፥ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር መወያየትን ዋና ዓላማው ያደረገ ነዉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ከአቡነ መርቆርዮስ ጋር ተገናኝተው የሚወያዩ ሲሆን፥ ሁለቱ ሲኖዶሶች እያካሄዱት ባለው እርቀ ሰላም ላይ በቦታው በመገኘት ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ታውቋል።