ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር እንዲቻል የፓን አፍሪካ ፓርላማ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቁ
አርትስ 14/02/2011
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በአፍሪካ ሃገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ ድጋፍ እንዲያደርግ ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡
በአጀንዳ 2063 የተካተተዉ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ባገባደድነዉ የፈረንጆቹ አመት ማርች 21 ላይ በ44 የአፍሪካ ሃገራት የተፈረመ ሲሆን እስካሁን ወደ ትግበራ ለመግባት 4 ሃገራት ፈርመዋል፡፡
ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ዘ ኒዉ ታይምስን ጠቅሶ እንደዘገበዉ የሩዋንዳዉ ፕሬዝዳንት ትናንት በኪጋሊ ከፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላት ጋር በነበራቸዉ ቆይታ በፍጥነት በመጓዝ ላይ የሚገኘዉን አሃጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና እዉን እንዲሆን ልታግዙን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
‘’እኛ አፍሪካዉያን ገንዘባችንንም ሆነ ጊዚያችንን አላግባብ ማባከን አንፈልግም’’ ስለዚህ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ተቋማትንና ባለድርሻ አካላትን በማወያየትና በማሳመን አሃጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናዉ በፍጥነት ተፈፃሚ እንዲሆን እንዲረዳን እንፈልጋለን ብለዋል ካጋሜ፡፡