loading
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የጀመራቸውን ስራዎች እንዲያጠናክር አሳሰቡ::

አዲስ አበባ፣የካቲት 26፣ 2013 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የጀመራቸውን ስራዎች እንዲያጠናክር አሳሰቡ:: ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲው 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ነው። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ቀዳሚ እንደመሆኑ ለአፍሪካዊያን ወንድምና እህቶች የትምህርት እድል በመስጠት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚዘነጋ አይደለም ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ይባል በነበረበት ወቅት ለአፍሪካ በመሪነት ደረጃ የተቀመጡ ተማሪዎችን ማፍራት መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር አገራዊ መፍትሄ እንደምትሻ ገልፀው በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በማኅበራዊ ዘርፎች ዩኒቨርሲቲው ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

የምስረታውን 70ኛ ዓመት ሲያከብር ስኬቶችን ብቻ ሳይሆን ጉድለቶቹ ላይማ በማተኮር የአገሪቷ የትምህርት ሁኔታ በሚጠበቀው ደረጃ ባለመሆኑ መፍትሄው ላይ መስራት አለበት ሲሉም አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለጥናትና ምርምር
የሚሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም በትምህርት ዘርፍ ፖሊሲ በማዘጋጀትና በተለያዩ ደረጃዎች የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ ጉልህ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል። በምርምር ዘርፍም ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙ ስራዎችን በግብርና፣ በጤናና ማኅበራዊ መስኮች ማካሄዱን ዘርዝረዋል።   ዩኒቨርሲቲው ለምርምር የሚሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱንና በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ኅብረት አባል ከመሆን ባለፈ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እውቅና ተሰጥቶታል ብለዋል።

ተቋሙ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ረገድ ትልቅ ስራ መስራቱን አንስተው ከተመሰረተ እስካሁን 250 ሺህ ተማሪዎችን በማስመረቅ የአገር መሪ፣ የኖቤል ሽልማት ያሸነፉ እና በሌሎችም ቦታዎች ውጤታማ ሰዎች ማፍራቱን ገልጸዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *