ፍርድ ቤቱ በሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቢ ህግ ለመጨረሻ ጊዜ ክስ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጠ
አርትስ 08/01/2011
በሰኔ 16ቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተፈፀመው የቦንብ ጥቃት በተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ላይ አቃቤ ህግ ለመጨረሻ ጊዜ ክስ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ይዞት በነበረው ቀጠሮ አቃቤ ህግ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው በነበሩት ባህሩ ቶላ፣ በየነ ቡላ፣ ጌቱ ግርማ እና ደሳለሽ ተስፋዬ ጨምሮ በስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ክስ ለመመስረት የ10 ቀን ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል።
አቃቤ ህግ ክሱን አጠናቆ ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ከታሰሩ 99 ቀናቸው መሆኑንና በየጊዜው ተጨማሪ ጊዜ እየተሰጠ መጉላላታቸውን ለፍርድ ቤቱ የተናገሩ ሲሆን ፍርድ ቤቱም አብዲሳ መገርሳና በየነ ቡላን በተመለከተ አቃቢ ህግ ክሱን አጠናቆ እንዲቀርብ ለመስከረም 14 ቀን 2011ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።