loading
ፋብሪጋስ ወደ ሞናኮ አቅንቷል

ፋብሪጋስ ወደ ሞናኮ አቅንቷል

በጥር የዝውወውር መስኮት በሰፊው ስሙ ከሞናኮ ጋር ሲያያዝ የነበረው ስፔናዊው አማካይ ተጫዋች ሴስክ ፋብሪጋስ በመጨረሻም ዝውውሩን አጠናቋል፡፡
ፋብሪጋስ ሞናኮን ለሶስት ዓመት ከግማሽ የተቀላቀለ ሲሆን በፈረንሳዩ ቡድን እስከ 2022 ሰኔ ወር ድረስ ቆይታውን ያደርጋል፡፡
ቼልሲዎች ሴስክ ፋብሪጋስ ወደ ሞናኮ የሚያደርገውን ዝውውር ሙሉ ለሙሉ አጠናቋል ሲሉ በድረ ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡
ከሰማያዊዎቹ ጋር ያለው ውል ሊጠናቀቅ የስድስት ወራት ጊዜ ቀርቶት የነበረው ስፔናዊው ተጫዋች፤ ቡድኑን በኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር በነበረው ግጥሚያ በአምበልነት እየመራ ሲያሸንፉ በደጋፊዎቹ ዘንድ በእንባ የታጀበ አሸኛኘት ተድርጎለታል፡፡
ሞናኮ በሊግ አንድ 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ፋብሪጋስ ደግሞ በቀድሞ የክለብ አጋሩ ቴሪ ሄንሪ ይሰለጥናል ማለት ነው፡፡
‹‹ሞናኮን በመቀላቀሌ ደስታ ተሰምቶኛል፤ ለእኔ አዲስ ፕሮጀክት ነው፣ ቡድኑ ብቃት ያላቸው ወጣት ተጫዋቾችን ከወጣት አሰልጣኝ ጋር የያዘ ነው›› ሲል ሴስክ ፋብሪጋስ ተናግሯል፡፡
ፋብሪጋስ በስታንፎርድ ብሪጅ አራት ዓመት ከግማሽ ቆይታ ሲያደርግ፤ ቼልሲ ሁለት የፕሪምየር ሊግ፣ የኤፍ ኤ ካፕ እና ሊግ ካፕ ዋንጫ ሲያሳካ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡
ቼልሲም ባወጣው መግለጫ ‹‹ሴስክ ፋብሪጋስን ለአስደናቂ አገልግሎቱ እናመሰግነዋለን፤ በሚቀጥለው የስራ ህይወት ምዕረፍም የተሻለ እንዲገጥመው መልካም ምኞታችን ነው›› በማለት ገልጧል፡፡
የፋብሪጋስ መልቀቅ ቼልሲንና ሳሪን ከጆርጊንሆ ጋር ለነበረው ጥምረት መሙያ የሚሆን ተጫዋች ለማፈላለግ ወደ ገበያ እንዲወጡ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል እየተጠቆመ ነው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *