ጥቃት አድራሾችን ከእንግዲህ አንታገሳቸውም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት “በንጹሃን ዜጎች ላይ በህገወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና የዜጎችን መተዳደሪያ ማውደም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒንሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን ሰላም እና ደህንነት መመለስ ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በታጣቂ ሃይሎች በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ የተፈጸመው ጥቃት እንዳይደገም መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአካባቢው በደረሰው ጥቃት የንጹሃን ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤ በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ አሁንም በአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት በመኖሩ ምክንያት ነዋሪዎች በአፋጣኝ የመንግስት ድጋፍ እንዲደርስላቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡