የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ተስፋዬ ኡርጌና አቶ ማርክስ ፀሃዬ ላይ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ አጠናቆ እንዲያቀርብ የ10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ተስፋዬ ኡርጌና አቶ ማርክስ ፀሃዬ ላይ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ አጠናቆ እንዲያቀርብ የ10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ
በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩትን አቶ ተስፋዬ ኡርጌና አቶ ማርክስ ፀሃዬን ጉዳይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት በትናንትናው ዕለት ተመልክቷል፤
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ የግራ ቀኙን ክርክር ከመርማሪ ፖሊስ ጅምር የምርመራ መዝገብ ጋር መዝኖ ያየው ችሎቱም፥ ከተስፋዬ ኡርጌ ጋር በተያያዘ አመልካች በተገቢ መልኩ ሪፖርት አላቀረበም፤ ይህም በተጠርጣሪው ላይ እሰራዋለሁ ያለውን ስራ በአግባቡ አለማከናወኑንና የተጠርጣሪውን የመከላከል ዕድል ማጥበቡን ተመልክቷል።
ፖሊስ ባቀረባቸው ማስረጃዎች ውስጥም ተጠርጣሪው ሰብዓዊ መብትን ባላከበረ መልኩ ምርመራ ያደርጉ እንደነበርና በስውር እስር ቤት ይገለገሉ እንደነበር ችሎቱ መረዳቱን አስታውቋል።
ተጎጂዎችን ለማናገርም በከፊል በክልል ከተሞች የሚገኙ በመሆናቸው እና ይህንን ማድረጉም የምርመራ መዝገቡን ለማጠናቀቅ ስለሚያስችል ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገዋል ሲል ችሎቱ ወስኗል።
ችሎቱ ከተጠርጣሪው ጋር በማይገናኙ ጉዳዮች ለጊዜ መጠየቂያነት የቀረቡ ምክንያቶችን ውድቅ በማድረግ ከተጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ ከታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የ 10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
ከማርክስ ፀሃዬ ጋር በተያያዘም ተከናወኑ የተባሉትም ሆነ ቀሪ ስራዎች ከሌላ መዝገብ ተገልብጠው መቅረባቸውን ችሎቱ የተገነዘበ ሲሆን ፖሊስ ትኩረት ሰጥቶ እንዳልሰራ የሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በቀጣይም ከዚህ አይነት ስራ እንዲቆጠብ ችሎቱ አሳስቧል።
በተጠርጣሪው ላይ ከተሰሙ አምስት ምስክሮች ውስጥ አራቱ ተጠራጣሪው ያለአግባብ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ፣ በድብቅ አስር ቤት እንዲቆዩና በሃይል ምርመራ እንዲደረግባቸው ያስደርጉ እንደነበር መመስከራቸውን ችሎቱ ተረድቷል።
ስለሆነም መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ የሁለቱን ተጠርጣሪዎች የምርመራ መዝገብ አጠናቆ እንዲያቀርብ ለጥር 2 ቀን 2011 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ፋና ዘግቧል።