የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜን ፈቀደ
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜን ፈቀደ
አርትስ 11/04/2011
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎት ትናንት ባዋለው ችሎት በቀድሞዎቹ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባልደረቦች አቶ ተስፋዬ ኡርጌ መዝገብ ተመልክቷል፤
መርማሪ ፖሊስ ያለውን መረጃ ለችሎቱ በማስረዳት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀን ጊዜ ጠይቆ በችሎቱ ተፈቅዶለታል።
አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በእስር ቦታ ላይ ሰብዓዊ መብቴ እየተጣሰ ነው በማለት ለችሎቱ አቤቱታ ያቀረቡ በመሆኑ ፖሊስ አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ተጠርጣሪው ደመወዛቸው በፍርድ ቤት ሳይታገድ እየተከፈላቸው አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳታቸው፤ መርማሪ ፖሊስ ጉዳዩ እንዲፈታ እንዲያግዛቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በሌላ ዜና በሜቴክ የንብረት ማሰባሰብና መልሶ መጠቀም ሃላፊ ሆነው ይሰሩ የነበሩት ኮሎኔል ካሳ ሮባ በትናንትናው እለት ፍርድ ቤት ቀረበዋል።
ያለፈው ዕሁድ በቁጥጥር ስር የዋሉት ኮሎኔል ካሳ፥ በተቋሙ በተጠቀሰው የሃላፊነት ቦታ ይሰሩ በነበረበት ወቅት፤ ማህበራትን በማቋቋምና ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር በርካታ ሃብት ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ እና መንግስትን በርካታ ሃብት ያሳጡ ናቸው በሚል መጠርጠሩን መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል። ተጠርጣሪው ኮሎኔል ካሳም በቀረበባቸው ክስ ላይ ራሳቸውን ተከላክለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ተመልክቶ ለፖሊስ የ7 ቀን ጊዜ በመስጠት ለታህሳስ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። መረጃው የኤፍ ቢ ሲ ነው፡፡