የፀጥታው ምክር ቤት በህዳሴው ግድብ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት የለውም-የናይል ተፋሰስ ሀገራት
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 1፣ 2013 የፀጥታው ምክር ቤት በህዳሴው ግድብ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት የለውም-የናይል ተፋሰስ ሀገራት
የናይል ተፋሰስ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚደረገው የግድቡ ድርድር ሂደት ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት ትክከለኛው መንገድ መሆኑን ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ድርድሩ ያለበትን ደረጃ በሚመለከት በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተፋሰሱ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ገለፃ አድርገዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸው ወቅት የላይኞቹ ሀገራት የአባይን ውሃ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት የመጠቀም ጉዳይ የጋራ ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ሂደትም ሱዳንና ግብፅ የአረብ ሊግ አባል ሀገራትን በማነሳሳት ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንዲሄድ በማድረግ አለማቀፋዊ ገፅታ እንዲኖረው መሞከራቸው ያልተገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ሁኔታውም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ የሚቃረን ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የልማት አጀንዳ እንደሆነ ኢትዮጵያ ታምናለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በፀጥታው ምክር ቤት የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
ምክር ቤቱም በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚካሄደውን የሶስትዮሽ ድርድር ማክበር አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የተፋሰሱ ሀገራትም ግብፅና ሱዳን እየተከተሉት ያሉትን ያልተገባ አካሄድ በጋራ እንዲቃወሙና እንዲያወግዙም ጥሪ አቅርበዋል አቶ ደመቀ፡፡
በገለፃው ላይ የተሳተፉት የተፋሰስ ሀገራት ተወካዮችም የጋራ በሆነው የውሃ ሀብት ዋነኛ ባለድርሻ አካል እንደመሆናችን መጠን፤ በኢትዮጵያ በኩል የግድቡን ሁኔታ በሚመለከት የተደረገችልን ገለፃ የሚደነቅና ሀገሪቱን የሚያስመሰግናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ዲፕሎማቶቹ የህዳሴ ግድብ የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት እንደሌለው በአፅንዖት መናራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡