የግድቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የወቅቱ ወሳኝ ጥያቄ ነው ::
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2013 በታላቁ የህደሴ ግድብ ግንባታ ዓለም አቀፍ የውሃ ህጎች ላይ የሚመክር 9ኛው ሃገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተጀመረ። ለሁለት ቀን በሚቆየው ጉባኤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዓለም አቀፍ የውሃ ህጎችን መሰረት ያደረጉ ሰባት ጥናታዊ ፅሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ድኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በጉባኤ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር የህደሴው ግድብ ለዘመናት ከተፈታተነን ድህነት ለመላቀቅ መንግስትና ህዝብ በጋራ የጀመሩት የህልውናችን መገለጫ ነው። ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ ሃገራት ጭምር ዘመን ተሻጋሪ ፀጋ የሚያላብስ ታሪካዊ ክንዋኔ መሆኑንም ተናግረዋል።
የታላቁ ህደሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ የአንድነታችንና የሉአላዊነታችን መገለጫ የታሪካችን አሻራ ነው ብለዋል። የግድቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የወቅቱ ጥያቄ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት
ዶክተር አስራት አፀደወይን ናቸው። ከጉባኤው ጎን ለጎን 3ኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀግብርን ታሳቢ ያደረገ የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ ተመላክቷል::