የዓለም ጤና ድርጅት አሁንም የአፍሪካ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገለፀ::
አዲስ አበባ፣ሐምሌ14፣ 2012 የዓለም ጤና ድርጅት አሁንም የአፍሪካ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገለፀ:: የድርጅቱ የአስከቸኳይ የጤና ነክ ጉዳዮች ሀላፊ የሆኑት ሚካኤል ሪያን በሰጡት መግለጫ መላው አፍሪካ የደቡብ አፍሪካን ሁኔታ ተመልክቶ መጠንቀቅ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከ373 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙባት ከ5 ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮቪድ19 ሳቢያ ህይታቸው አልፏል፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ ሀብታም በሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የጀመረው የቫይረሱ ስርጭት አሁን ወደ ድሃዎቹም መሸጋገሩ ችግሩን የባሰ ከባድ ያደርገዋል ብለዋል ሀላፊው፡፡ አለልጀዚራ እንደዘገበው በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የቫይረሱ ስርጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 69 በመቶ መጨመሩ ተስተውሏል፡፡ ይሄ ደግሞ በአህጉሩ በሽታው በፍጥነት እያደገ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎ መዘናጋትን ማስወገድ አለባቸው ነው የተባለው፡፡ በአፍሪካ የቫይረሱ ስርጭት ከሌላው ዓለም ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ቢመስልም ሲጀምር የነበረው እና አሁን ላይ ያለው ፍጥነት ሲወዳደር ግን የአሁኑ በእጅጉ ያስከነዳዋል ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት፡፡ አሁን ላይ በአፍሪካ ከ740 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከነዚህም መካከከል ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሞተዋል፡፡ ከቫይረሱ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 392 ሺህ 377 መድረሱን ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡