የዓለም ጤና ድርጅት በቀጣዮቹ አምስት ወራት በኮቪድ 19 የሚያዙ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ ያድጋል ሲል አሳሰበ፡፡
አዲስ አበባ፣ሐምሌ29፣ 2012 የዓለም ጤና ድርጅት በቀጣዮቹ አምስት ወራት በኮቪድ 19 የሚያዙ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ ያድጋል ሲል አሳሰበ፡፡በዓለም አቀፍ የሚገኙ እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ በሶስት እጥፍ ያድጋል ብሏል ድርጅቱ፡፡
በቫይረሱ ስርጭት የመጀመሪያውን ስፍራ የያዘቸው አሜሪካን ጨምሮ ስፔን፣ጀርመን፣ ፈረንሳይና ጃፓን አዲስ በቫይረሱ ከሚያዙት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ወጣቶች መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ አኳያ ቸልተኝነት እንደሚታይባቸው ነው የጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ጥናት የሚያስረዳው፡፡
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዳግም መጀመርና ወጣቶች ወደ ስራ መመለሳቸው እንዲሁም የባህርዳርቻ እና የምሽት መዝናኛ ቤቶች መከፈት ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፊያ መንገድ ናቸው ተብሏል፡፡የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሰጡት መግለጫ ከዚህ ቀደም ለማለት እንደሞከርነውና አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ወጣቶች በቫይረሱ ይያዛሉ፣ ይሞታሉ ለሌሎችም ያስተላልፋሉ ብለዋል፡፡በመሆኑም ሀገራት ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የመከላከል ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ዋና ዳሬክተሩ ያሳሰቡት፡፡
በአብነት ታምራት