የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ከኦነግ ጋር ያደረግኩት ስምምነት እስካሁን ተግባራዊ መሆን አልቻለም አለ
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ከኦነግ ጋር ያደረግኩት ስምምነት እስካሁን ተግባራዊ መሆን አልቻለም አለ
አርትስ 17/04/11
ኦዲፒ እንዳለው ከኦነግ ጋር አብሮ ለመስራት ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ቢዋቀርም በኦነግ በኩል በተፈጠረው ክፍተት ከእቅዱ አብዛኛው ተግባር እስካሁን ተፈጻሚ አልሆነም።
በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) በኩል የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሞገስ ኤደአ እንደተናገሩት ኮሚቴው የተቋቋመው የሃገር ሽማግሌዎች ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ነበር።
አቶ ሞገስ እንደሚሉት ለተያዘው እቅድ አለመፈጸም ምክንያቱ ኦነግ ከመንግስት ጋር እንዲሰራ ስምምነት የደረሰባቸውን ጉዳዮች በሙሉ ተፈጻሚ አለማድረጉ ነው።
ከእቅዶቹ መካከል የታጠቁ አካላት ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግና በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መጣር የሚሉት ቀዳሚ ተግባራት ነበሩ ።
ይሁን እነጂ በኦነግ በኩል ሰራዊቱ ትጥቅ ባለመፍታቱ በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች ምክንያት ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ እና በመንግስት መዋቅሮች ህዝቡ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ከኮሚቴው እቅዶች ውስጥ ተካትተው ነበር።
እንደአቶ ሞገስ ገለጻ የጋራ እቅዶቹ በሙሉ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲፈጸሙ ኦዲፒ ፍላጎት ነበረው።
ነገር ግን ኦነግ ለእቅዱ አፈጻጸም 15 ቀን ጊዜ በመጠየቁ በዚሁ ላይ ስምምነት ተደርሶ ከህዳር 17 ጀምሮ ወደስራ ተገብቶ ነበር።
እስካሁን ባለው የእቅድ አፈፃፀም በኦዲፒ በኩል አብዛኛው ስራ የተፈጸመ ቢሆንም በኦነግ በኩል ግን ከኤርትራ የገቡ 1 ሺህ 300 የጦር አባላቱን ለመንግስት ከማስረከብ እና ምእራብ ኦሮሚያ ላይ ያለውን የታጠቀ ሀይል ከማወያየት ባለፈ የተሰራ ስራ የለም ነው ያሉት አቶ ሞገስ።
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሰው ህይወት መጥፋቱንና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም መዘጋታቸውን አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በኩል ያለው ኮሚቴ በእቅድ አፈፃፀሙ ዙሪያ መግለጫ እንዲሰጥ ጥሪ ቢደረግለትም በስፍራው እንዳልተገኘ ነው የተገለፀው።