የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ።
ልዑኩ ወደ ሀገር ቤት የመጣውም በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መካከል ባሳለፍነው ነሃሴ 1 2010 ዓ.ም የእርቅ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ነው።
ልዑኩ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የኦህዴድ የከተማ ፖለቲካና የድርጅት ዘረፍ ሀላፊ አቶ ከፍያለው አያና እናሌሎች የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውለታል።
የልዑካን ቡድኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኣባልና የድርጅቱ ቃል ኣቀባይ በሆኑት ኣቶ ቶሌራ ኣደባ ተመርቶ ነው ወደ ሀገር ቤት የገባው።
የኦነግ ልኡክ ዛሬ ከሰዓት አዲስ አበባ መግባታቸውን የኦህዴድ የከተማ ፖለቲካና የድርጅት ዘረፍ ሀላፊ አቶ ከፍያለው አያና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የእርቅ ስምምነት ባሳለፍነው ነሃሴ 1 2010 ዓ.ም በኤርትራ አስመራ መፈራረማቸው ይታወሳል።
በወቅቱም በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና በኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑክ ወደ አስመራ በማቅናት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራውና ልዑክ ጋር የእርቅ ውይይትም አካሂዷል።
በዚህም ኦነግ ለበርካታ ዓመታት ሲያካሄድ የቆየውን የትጥቅ ትግል በማቆም በሀገሪቱ በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ለመቀጠል ከስምምነት ተደርሷል።
ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ስራ ተግባራዊ ለማድረግና ምርመራና ጊዜ የሚጠይቁትን በሂደት ከፍጻሜ የሚያደርስ ኮሚቴ በአስቸኳይ ለማቋቋም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
እንዲሁም አንድ የኦነግ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዝ የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ መግለፃቸውን ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ነው በዛሬው እለት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ልኡክ አዲስ አበባ የገባው።
በቅርቡ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7 ከሽብርተኝነት ዝርዝር መሰረዙ ይታወሳል።
ኤፍ.ቢ.ሲ