loading
የእስያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ይከናወናል

የእስያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ይከናወናል

ከጥር 5/2019 ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረው 17ኛው የእስያ ዋንጫ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡

 

ውድድሩ በ24 ቡድኖች መካከል ላለፉት አራት ሳምንታት አካባቢ ሲከናወን የቆየ ሲሆን የጃፓን እና ኳታር ብሔራዊ ቡድኖች አቡ ዳቢ ላይ በተሰየመው የዛይድ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም የውድድሩን ዋንጫ ለማንሳት ተፋጥጠዋል፡፡

ጃፓን በግማሽ ፍፃሜው ኢራንን 3 ለ 0 በመርታት ለፍፃሜው ውድድር ስትበቃ፤ በውድድሩ አመርቂ ጉዞን ስታደርግ የነበረችው ኳታር ውድድሩን የደገሰችውን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ድል በማድረግ ነው የዋንጫ ተፋላሚነቷን ያረጋገጠችው፡፡

እስካሁን በተከናወኑ 16 ውድድሮች በብዛት ማሸነፍ የቻለችው ጃፓን ስትሆን ለፍፃሜ የደረሰችባቸውን አራት ውድድሮች በሙሉ በድል ተወጥታለች፡፡

በአንድ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ከመሳተፍ ውጭ ታሪክ የሌላት ኳታር በውድድሩ ካሳየችው አቋም አንፃር ለመጀመሪያ ጊዜ በደረሰችበት የፍፃሜ ግጥሚያ ጥሩ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እአ.አ በ1956 ዓ/ም በተጀመረው የእስያ ዋንጫ፤ ከጃፓን በመቀጠል ሳውዲ አረቢያና ኢራን ሶስት ጊዜ ያህል አሸንፈዋል፡፡

ለኳታር የሚጫወተው ትውልደ ሱዳናዊው አጥቂ አልሞኤዝ አሊ የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በ8 ጎሎች እየመራ ይገኛል፡፡

የውድድሩ አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን የዋንጫ እና የአምስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል፤ የፍፃሜ ተፋላሚው 3 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ቡድኖች የአንድ ሚሊየን ዶላር ሽልማት ይበረክትላቸዋል ተብሏል፡፡

ሁሉም ተሰታፊ 24 ብሔራ ቡድኖች ደግሞ እያንዳንዳቸው የ200 ሺ ዶላር ያገኛሉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *