የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመር፤ ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ ቀጥለው ይካሄዳሉ
የሳምንቱ መርሀግብር ጨዋታዎች ዛሬ በሲዳማ ቡና እና ስሑል ሽረ መካከል ተካሂዶ፤ ባለሜዳው ሲዳማ 3 ለ 2 አሸንፎ ሁለተኛ ደረጃን ከፋሲል ተረክቧል፡፡ አዲስ ግደይ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ሁለት እና ዳዊት ተፈራ የድል ግቦችን ሲያስቆጥሩ ፤ ሳሊፍ ፎፋና የሽረን ሁለት ግቦች ከመረብ አገናኝቷል፡፡
በነገው ዕለት ደግሞ አራት ያህል ግጥሚያዎች አዲስ አበባ እና ክልል ላይ ይከናወናሉ፤ ክልል ስታዲየሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9፡00 ሰዓት ይደረጋሉ፡፡
ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ በደቡብ ደርቢ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ወላይታ ድቻን ይገጥማል፡፡
የምስራቅ ኢትዮጵያው ድሬዳዋ ከነማ ሜዳው ላይ መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያስተናግዳል፡፡ የወልዋሎው አሰልጣኝ ዩሀንስ ሳህሌ የቀድሞ ክለቡን ድሬዳዋ የሚገጥሙ ይሆናል፡፡
የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው ደደቢት ደግሞ በትግራይ ስታዲየም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ይጫወታል፡፡
በሳምንቱ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል በጉጉት የሚጠበቀው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከነማ መካከል 10፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ባህር ዳር ላይ የጣናው ሞገድ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ዕሁድ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ የሊጉ አናት ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ትግራይ ስታዲየም ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ሁለቱም ቡድኖች ከሽንፈት መልስ 9፡00 ሰዓት ላይ ይፋለማሉ፤ በተመሳሳይ ሰዓት በስቱዋርት ሃል የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ከከተማው ቡድን ጋር ይጫወታል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ባደረጉት የሊግ ጨዋታ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው የተመለሱ በመሆኑ በጥሩ ስነ ልቦና ላይ ይገኛሉ፡፡
በዕለቱ 10፡00 ላይ ደግሞ ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር የተለያው መከላከያ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ፋሲል ከነማን ያስተናግዳል፡፡ የጦሩ ቡድን ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ፤ አፄዎቹ ወደ ሊጉ መሪ መቐለ ለመጠጋት ድል ያስፈልጋቸዋል፡፡