የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ቀጥለው ይካሄዳሉ
በ18ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃግብር በዕለተ ቅዳሜ አንድ ጨዋታ ብቻ ይደረጋል፡፡
በተከታታይ ድሎች ከወራጅ ቀጠና መውጣት የቻለው ደቡብ ፖሊስ ወደ ትግራይ አቅንቶ ከደደቢት ጋር 9፡00 ላይ የሚጫወት ይሆናል፡፡
የሳምንቱ ቀሪ በርካታ ጨዋታዎች በሰንበት በተመሳሳይ 9፡ 00 ሲከናወኑ፤ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የተሰኘው ግጥሚያ ጎንደር ላይ በፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ መካከል ይደረጋል፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሊግ የተመሳሳይ ሰዓት ጨዋታዎች ፤ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ አዳማ ከተማን ድል አድርጎ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጅማ ተጉዞ የአምናውን የሊጉ ሻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋርን ይገጥማል፡፡
አዳማ ከተማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የትግራዩን ስሑል ሽረ የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
የአማራ ክልሉ ክለብ ባህርዳር ከተማ በግዙፉ የባህር ዳር ስታዲየም በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን ሲዳማ ቡና ይጋብዛል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች በደቡብ ደርቢ ወላይታ ድቻ ሶዶ ላይ ሃዋሳ ከተማን ይገጥማል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሰሜን አቅንቶ በትግራይ ስታዲየም ከዩሃንስ ሳህሌው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ድልን እያሳደደ ሶስት ለማግኘት ይጫወታል፡፡ ምስራቅ ኢትዮጵያ ላይ ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው መከላከያን የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡ የሊጉን የደረጃ ሰንጠራዥ መቐለ 70 እንደርታ በ39 ነጥብ ይመረዋል፤ ሲዳማ ቡና በ31 ይከተላል ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ በተመሳሳይ 29 ነጥቦች ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ መከላከያ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የመቐለው አማኑኤል ገብረሚካኤል እና የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በ11 ጎሎች ይመሩታል፤ አዲስ ግደይ ከ ሲዳማ ቡና በ10 ይከተላቸዋል፡፡