የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ግጥሚያዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ግጥሚያዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
የሊጉ የመጀመሪያ ዙር የ15ኛ ሳምንት ግጥሚያዎች ዕሁድ፣ ሰኞና ማክሰኞ ይከናወናሉ፡፡
ዛሬ ሶስት ያህል ግጥሚያዎች በክልል ስታዲየሞች ላይ ሲካሄዱ፤ በጳውሎስ ጌታቸው የሚመራው ባህር ዳር ከነማ በግዙፉ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አዳማ ከተማን 9፡00 ሲል ያስተናግዳል ፡፡
በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ደደቢት በትግራይ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማን በተመሳሳይ ሰዓት የሚገጥም ይሆናል፤ ሌላኛው ክልል ላይ የሚከናወነው ጨዋታ በእንግሊዛዊው ስቱዋርት ሃል የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አቅንቶ በሶዶ ስታዲየም ከወላይታ ድቻ ጋር 9፡00 ሲል ይፋለማል፡፡
ፈረሰኞቹ የሊጉ አናት ላይ ሆነው ለመጨረስ፤ ይህን ጨዋታ በድል ተወጥተው፤ ቀሪ ጨዋታ ያላቸውን ቡድኖች የሚያስመዘግቡትን ውጤት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ግጥሚያው 9፡00 ላይ ሲከናወን አርቢትር ዮናስ ካሳሁን በመሀል ዳኝነት ይመሩታል ተብሏል፡፡
የሊጉ መርሀግብር በዕለተ ሰኞ ሲቀጥል ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፤ ከሽንፈት መልስ ወደ ጎንደር የተመለሰው ፋሲል ከናማ በሜዳው ፋሲለደስ ስታዲየም ስሑል ሽረን ያስተናግዳል፤ ግጥሚያው ቀን 9፡00 ላይ ይጀመራል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ሌላኛው ክልል ላይ የሚካሄደው ግጥሚያ ትግራይ ስታዲየም ላይ በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ሲዳማ ቡና መካከል ይከናወናል፡፡
ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ ደግሞ በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል፡፡
ማክሰኞ በሊጉ ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው የትግራዩ መቐለ 70 እንደርታ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ አቅንቶ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ይፋለማል፡፡
የ15ኛው ሳምንት የመጨረሻ ፍልሚያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው መከላከያ በዲዲዬ ጎሜዝ የሚመራውን ኢትዮጵያ ቡና ይገጥማል፡፡ ጨዋታው ለዛሬ መርሀግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ምክንያት ለማክሰኞ ተላልፏል፡፡ በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መቐለ እና ሲዳማ በዕኩል 26 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፤ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ አራተኛ ላይ ይገኛል፡፡
ስሑል ሽረ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ ፡፡
የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ምንይሉ ወንድሙ ከመከላከያ በ11 ጎሎች ሲመራ፤ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቐለ 70 እንደርታ እና አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና በ9 ጎሎች ይከተላሉ፡፡