loading
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ሁለቱም ፓትርያርኮች በእኩል የአባትነት ክብር እንዲያገለግሉ ተወሰነ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ሁለቱም ፓትርያርኮች በእኩል የአባትነት ክብር እንዲያገለግሉ ተወሰነ።
ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን የሰላምና የእርቅ ጉባዔው ተከትሎ የተወሰኑ ውሳኔዎች ይፋ ሆነዋል።
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር እንድተመራ የተወሰነ ሲሆን፥ በሁለቱም ሲኖዶሶች የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ ምልዓተ ጉባኤ ይፈታል ተብሏል።
የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች ስም ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሳም ነው ውሳኔ የተላለፈው።
ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወት እስካሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያቲያኗን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንድትይዝ የሚለው ውሳኔ ከተላለፈባቸው ነጥቦች መካከል ይገኛል።
በውሳኔው መሰረት ስደተኛውን ሲኖዶስ ሲመሩ የቆዩት አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሀገር ይመለሳሉ።
በመሆኑም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሕገ ቤተክርቲያን መሠረት የአስተዳደር ሲሰሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ደግሞ በጸሎት እና በቡራኬ ቤተክርስቲያንን እንዲመሩ ይደረጋል ነው የተባለው።
የቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ሆነ በውስጥ በሀገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሀላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ የእምነቱ ተከታዮች በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልኡካኑ ጉባዔ ወስኗል።
ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተፈቶ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ጉባዔው እንደወሰነ ታውቋል።
ከልዩነት በኋላ ስለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት በተመሳሳይ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭና በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ተወስኗል።
በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል በተፈጠረው ችግር ምክንያት የተላለፈው ቃለ ውግዘት ከዚህ ስምምነት በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ መወሰኑ ተነግሯል።
ከዚህ ባለፈ የየሀገሩን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ የቃለ ዓዋዲውና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ገዥነት የሚረጋገጥበት መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚያዘጋጅም ተጠቁሟል።
እንዲሁም በውጭ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በመዋቅራዊ አስተዳደር መሠረት ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በመቀበል በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንድትመራም ተወስኗል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና የሁለቱንም ሲኖዶስ መዋሐድ ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም በስደት የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ወደ ሀገር ተመልሰው በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ኹኔታ የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡካን እንዲያዘጋጁና እንዲከታተሉ መወሰኑን የወጣው መግለጫ ያመለክታል።
ምንጭ ፦ ኤፍ. ቢ. ሲ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *