የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከማሊ አቻው ጋር በአቻ ውጤት ተለያየ፡፡
እ.አ.አ በ2020 ጃፓን ለምታሰናዳው የኦሎምፒክ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ሀገራት በየአህጉራቸው የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው፡፡
ኢትዮየጵያ አፍሪካን ከሚወክሉ ሶስት ሀገራት አንዱ ለመሆን የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን በዛሬው ዕለት ከማሊ ጋር አካሂዳ ሙሉ ጨዋታው በ 1 ለ 1 አቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በሁለቱም ብሔራ ቡድኖች በኩል ግብ ያልተስተናገደ ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ቀዳሚውን ግብ እንግዳው የማሊ ቡድን በዲያዴ ዲያንካ አማካኝነት ሲያስቆጥር፤ የኢትዮጵያን የአቻነት ግብ ከ20 ደቂቃ ቆይታ በኋላ የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጫዋቹ ደስታ ደሙ አስቆጥሯል፡፡
የእለቱን ጨዋታ ናሚቢያዊያን ዳኞች መርተውታል፡፡
ሙሉ ጨዋታውም በዚሁ የአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ፤ የመልሱ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ የማሊ መዲና ባማኮ ላይ በሚገኘው ሞዲቦ ኬይታ ስታዲየም ላይ ይደረጋል፡፡