loading
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ የከፍያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየደረግኩ ነው አለ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ የከፍያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየደረግኩ ነው አለ።

አዲሱ አሰራር ደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸው በዘመናዊ መንገድ ለመፈፀም የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ተግባራዊ ይሆናል በተባለው በዚሁ አዲስ የክፍያ አሰራር ተጠቃሚ የሚሆኑት የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ማለትም ሁሉም የኢንዱስትሪ ደንበኞች፣ የግል ድርጅቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሲሆኑ፤በተጨማሪም ማንኛውም ፍቃደኛ የሚሆን የዝቅተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞችም በአሰራሩ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይናገራል።

አገልግሎቱ ለአርትስ ቴሌቪዥን በላከው መግለጫ እንደጠቀሰው ዘመናዊ የክፍያ ስርዓቱ ዘመናዊ አሰራርን የሚከተል በመሆኑ ለደንበኞች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉም ባለፈ ደንበኞች ለወራዊ ክፍያ የሚያባክኑት ጊዜ ይታደጋል ነው የተባለው፡፡

ከዚህ ባለፈም የተቋሙንና የደንበኞችን መረጃ በጥንቃቄ ለመያዝ የሚያስችል ሲሆን አሰራሩ በደረሰኝ የሚከናወን በመሆኑ ለክትትልና ቁጥጥር አመቺ ነው ይላል የአገልግሎቱ መግለጫ ።

በተጨማሪም ደንበኞች መረጃቸውን በተመለከተ በኢሜይልና በአጭር የጽሑፍ መልዕልት ከተቋሙ የሚደርሳቸው ሲሆን ይህም ደንበኞች የክፍያ ጊዜ በሚያልፋቸው ወቅት የሚፈጠረውን የጊዜና የገንዘብ ብክነት ያስቀራል፡፡

ደንበኞች ከሂሳባቸው ተቀኛሽ የተደረገው ገንዘብ መረጃ ተቋሙ ደረሰኝ የሚያዘጋጅላቸው ሲሆን፤ ከሂሳባቸው ተቀናሽ ስለተደረገው ገንዘብ መረጃም በባንኩ በኩል የአጭር የጽሑፍ መልዕት ይደርሳቸዋል ነው የተባለው።

በአሁኑ ወቅት የደንበኞችን መሰረታዊ መረጃዎች የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ አሰራሩ ተግባራዊ የሚደረገው ደንበኞች የሚጠበቅባቸው መረጃዎች ከሰጡና ከተቋሙ ጋር ስምምነት ከፈፀሙ በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞችና ፍቃደኛ የሆኑ የዝቅተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመሄድ ስምምነታቸውን በተዘጋጀው ቅፅ እንዲሞሉ ተቋሙ ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞቹ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በባንክ እንዲከፍሉ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም መፈራረሙ ይታወሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *