የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባለ ስልጣናት ግድያ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የመከላከያ ምስክሮችን መስማት ጀመረ፡፡
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6፣ 2013 የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባለ ስልጣናት ግድያ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የመከላከያ ምስክሮችን መስማት ጀመረ፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያ እጃቸው አለበት በተባሉት በእነሻምበል መማር ጌትነት መዝገብ የተከሰሱ 32 ተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮች ነው ማዳመጥ የጀመረው፡፡
በዚሁ የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ ከነበሩት 55 ተከሳሾች መካከል 20ዎቹ ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ መደረጉ ይታወሳል።
በዋና ወንጀል ፈጻሚነት በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው ሲታይ የቆየው አንደኛ ተከሳሽ ሻምበል መማር ጌትነት፣ 15ኛ ተከሳሽ በላይነው ሰፊነው እና 44ኛ ተከሳሽ ልቅናው ይሁኔ ላይ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ከአሁን ቀደም የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ይህም በወንጀል ድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው በሰውና በአቃቤ ህግ ማስረጃ በመረጋገጡ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
የቀሩት 32 ተከሳሾች ደግሞ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ቀነ ቀጠሮ መሰረት ነው የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት የጀመሩት፡፡
አቃቤ ህግ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቧቸው አብዛኞቹ የመከላከያ ምስክሮች በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች በመሆናቸው እንዳይመሰክሩ ህጉ ስለሚከለክል ሊመሰክሩ አይገባም የሚል መቃወሚያ አቅርቧል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው አንደኛው ተከሳሽ ለሌላኛው ተከሳሽ እንዳይመሰክር የሚከለክል ህግ የሌለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን መቃወሚያ ውድቅ በማድርግ የመከላከያ ምስክሮቻችን ይሰሙልን ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ አንደኛው ተከሳሽ ለሌላኛው ተከሳሽ እንዳይመሰክር የሚከለክል ህግ የሌለ መሆኑን አቃቤ ህግ ያቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ እንዳደረገው ኢዜአ ዘግቧል፡፡