የትግራይ ክልል መንግስት የአማራ ክልል መግለጫ መሰረታዊ የህግ ጥሰት አለበት አለ
በራያ አካባቢ የተከሰተው ግጭት መነሻ የማንነት ጥያቄ ነው በማለት የአማራ ክልላዊ መንግስት
ያወጣው መግለጫ የህገመንግስቱን ድንጋጌ የጣሰ ነው ሲል የትግራይ ክልላዊ መንግስት ወቀሰ።
ሕገ መንግስቱ በማንነት ጉዳይ ላይ ያስቀመጠውን ስርዓት በመጣስ በሌላ ክልል የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ
መግባቱን የሚያረጋግጥ መግለጫ ነው ሲልም ኮንኖታል፡፡
የትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እንዳስነበበው የአማራ ክልል መንግስት ያወጣው መግለጫ
መሰረታዊ የሆነ የሕገ መንግስት ጥሰት ያለበት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረውን አብሮነት የሚጎዳ አደገኛ
አካሄድ ነው ብሎታል።
በመሆኑም በአስቸኳይ እንዲታረም እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም የትግራይን ህዝብ በይፋ
ይቅርታ እንዲጠይቅ ነው ያሳሰበው።
የአማራ ክልላዊ መንግስት አስቀድሞ በሰጠው መግለጫው ከትግራይ ብሔራዊ ክልል ጋር
በሚያዋሰኑት የወልቃይትና የራያ አላማጣ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሰላም መታወክ መከሰቱን
እና ሁኔታው ለክልሉ ትልቅ የፀጥታ ስጋት መሆኑን ገልጾ ነበር።
በአዋሳኝ ክልሎች የሚፈጠረው ግጭት የሌላ ክልል ጉዳይ ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ተሻጋሪነት
ያለው ሁላችንንም የሚያውክ የሰላም ጠንቅ በመሆኑ መፍትሄው የሃይል እርምጃ መውሰድ ሳይሆን
ጥያቄውን ከሚያነሳው የአካባቢው ህዝብ ጋር የሰከነ ውይይት ማድረግ ነው በማለት አሳስቦም
እንደነበር አይዘነጋም።
የትግራይ ክልል በዛሬው መግለጫው ትግራይ ዜጎች በማንነታቸው የሚፈናቀሉባትና የአማራ ክልል
ሰላም ችግር ፈጣሪ መባሏ አሳዛኝና ከትንኮሳ የማይተናነስ ጠብ አጫሪ አቋም ነው በማለት ኮንኗል።