የትምህርት ሚኒስቴር የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ አድራጎት መርሀ-ግብር በይፋ ተጀመረ::
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29፣ 2013 የትምህርት ሚኒስቴር የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ አድራጎት መርሀ-ግብር በይፋ ተጀመረ::
የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስ በትምህርት ዘርፉ የሚካሄደውን የክረምት የበጎ አድራጎት መርሀ-ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።
በበጎ አድራጎት መርሀ ግብሩም በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ በክፍለ ከተማው 15 የአቅመ ደካሞች ቤት እንደሚታደስም ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነው የመተጋገዝ እና የመደጋገፍ ባህልን መሰረት በማድረግ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ በመቻላችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
በሁለት ሳምንት ውስጥም ቤቶቹን አድሰው ለነዋሪዎቹ እንደሚያስረክቡም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ለአቅመ ደካሞቹም ቤቱን ከማደስ ባሻገር አስፈላጊ የቤት እቃዎችም እንደሚሟሉ ተገልጿል።
ተማሪዎች በክረምቱ መርሀ-ግብር በየአካባቢያቸው በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ ከወገን አልፈው ሀገርን የማገዝ ሀላፊነታቸውን በንቃት እንዲወጡም ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።