የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማፋጠን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጂኢ ሃይድሮ ፍራንስ ከተባለ ኩባንያ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ግንባታ ለማፋጠን የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙ ተገለጸ፡፡
ጃኢ ሃይድሮ ፍራንስ በቅድሚያ ሃይል እንዲያመነጩ ታስበው ዲዛይን የተደረጉትን ሁለት ተርባይኖችን ጨምሮ አምስት የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ለማምረት፣ ለመግጠምና ለመፈተሸ ኮሚሌክስ ከተባለ ድርጅት ጋር በጥምረት የ53 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ፈርሟል።
ጂኢ ሃይድሮ ቀደም ሲል ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ተርባይን ጄኔሬተሮችን ለማቅረብ ብቻ የንዑስ ተቋራጭነት ስምምነት እንደነበረው የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ስምምነት የማምረት፣ የተጓደሉ አቅርቦቶችን የማሟላት፣ የተከላና የፍተሻ ሥራዎችን ያከተተ ነው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ የብረታ ብረት ሥራዎችን ሲኖ ሃይድሮ ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር ጋር ለመፈራረም ድርድሮች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል፡፡
ኩባንያው የኃይል ማመንጫ የውሃ ማስተላፊያ ቱቦዎችን፣ የመቆጣሪያ እና የጎርፍ ማስተንፈሻ በሮችን የመገንባትና የማስተካከል ስራ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል፡፡
ሲኖ ሃይድሮ የሚሰራው ሥራ የሲቪል ስራዎችን በማፋጠን ከአጠቃላይ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ሁለቱ አስቀድመው ኃይል እንዲያመነጩ ያግዛል ተብሏል፡፡
በተያያዘም በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ በዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ የተመራ የልዑካን ቡድን የግድቡን የሲቪልና የብረታ ብረት ስራዎች ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የግንባታው አማካሪዎች ትራክትቤል ኢንጂነሪንግና ኤልክ ኤሌክትሮ ኮንሰልት ተወካዮች በግድቡ ግንባታ ላይ ለታዩት ችግሮች ቴክኒካዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች ስለመከናወናቸው አንስተዋል፡፡
ቀደም ሲል የተጀመሩና የተከናወኑ ከብረታ ብረት ጋር የተያያዙ ስራዎች ከ90 በመቶ በላይ ፍተሻ ተደርጎ ችግሮቹን ለማረም የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የግድቡን ስራዎች ተዟዙረው የተመለከቱት ሚኒስትሩና ዋና ስራ አስፈጻሚው ግንባታውን ለማፋጠን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልን ጠቅሶ ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡