የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ወደ ጨረቃ ጉዞ በማድረግ የመጀመሪያዋ የአረብ ሀገር ልትሆን ተዘጋጅታለች ተባለ::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2013 የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ወደ ጨረቃ ጉዞ በማድረግ የመጀመሪያዋ የአረብ ሀገር ልትሆን ተዘጋጅታለች ተባለ::ጠቅላይ ሚስትርና የአቡዳቢ አስተዳዳሪ የሆኑት ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሽድ አል መክቱም በቱይተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ሀገራቸው የጠፈር መንኮራኩር ወደ ጨረቃ ለመላክ መዘጋጀቷን ይፋ
አድርገዋል፡፡
አቡዳቢ በቅርቡ ወደ ማርስ ሳተላይት ያመጠቀች ሲሆን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2024 መንኮራኩር ጨረቃ ላይ ለማሻረፍ እቅድ ይዛ እየሰራች ነው ተብሏል፡፡ ጨረቃን የማሰሱ ስራ እንዲሳካ ሁሉንም ተግባር ያከናወኑት የሀገራችን ኢንጂኔሮች ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው አቡዳቢ እቅዷን በተባለው ጊዜ ማሳካት የምትችል ከሆነ ወደ ጨረቃ ጉዞ በማድረግ ከዓለማችን አራተኛ ከአረቡ ዓለም ደግሞ የመጀመሪያዋ ሀገር በመሆን አዲስ ታሪክ ታስመዘግባለች፡፡
ከአሁን ቀደም ጨረቃን በማሰስ ቀዳሚዎቹ ሀገራት አሜሪካ፣ ሩሲያና ቻይና ሲሆኑ ህንድ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ያመጠቀቻት መንኮራኩር ከ400 ሚሊዮን ኪሎሜትር ጉዞ በኋላ ማርስ ውስጥ ያለውን የከባቢ አየር ሁኔታ እንድታጠና ተልዕኮ እንደተሰጣት ተነግሯል፡፡