loading
የቀድሞው የሶማሌ ሰክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት መስኮት ሰብረው ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ሲል ፖሊስ ገለጸ

አቶ አብዲ ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀጠሮ ችሎት በቀረቡበት ወቅት መርማሪ ፖሊስ እንደገለጸው አቶ አብዲ መሐመድ ለደህንነታቸውና ለጤናቸው ሲባል የፖሊስ ቢሮ ውስጥ ታስረው ነበር።

ይሁንና አቶ አብዲ የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና አንድ የጥበቃ አባልን ጉሮሮ በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ብሏል።

አቶ አብዲ መሐመድ በበኩላቸው ድርጊቱ ሆን ብሎ ስሜን ለማጥፋትና እኔን ለመምታት የተደረገ ሴራ ነው ብለዋል።

ድርጊቱን ፈጽመዋል መባሉ ውሸት መሆኑንና በእርሳቸው ላይም ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ  ተናግረዋል።

ምቹ ባልሆነ እስር ቤት መታሰራቸውን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነ ታሳሪ የታሰሩበትን ክፍል በር ገንጥሎ በመግባት ሁለት ቀን ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሞከረና ይህም በደህንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አቶ አብዲ መሐመድ ማንኛውም እስረኛ በሚቆይበት እስር ቤት እንደታሰሩ ገልጸው በእርሳቸው ላይ ምንም አይነት የተለየ ጫና እየተደረገ እንዳልሆነ አስታውቋል።

በተጨማሪም ፖሊስ ከእርሳቸው ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ለግጭቱ መቀስቀስ ተጠያቂ መሆናቸውንና በዚህም ተጸጽተው ይቅርታ መጠያቃቸውን ገልጿል።

ፖሊስ በአብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ምርመራውን እያካሄደ ያለው ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ በማሳሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *