የሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሶብናል ያሉ 300 የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት ፤ዲያቆናትና አገልጋዮች ፍትህ ማግኘታቸዉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ካህናቱ ከአስተዳደረዊ በደል በተጨማሪም ከስራ መባረር፤ የደሞዝ ክፍያን አለማግኘት፤ ያለቅድመ ዝግጅትና ፍትሃዊ ያልሆነ ዝውውር እንዲሁም ያለ ስራ መንገዋልል ከዋነኞቹ የመብት ጥሰቶች እንደሚካተቱ ቅሬታው የደረሰው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተናግሯል፡፡
በኮሚሽኑ የከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድሜነህ ዘውዱ እንዳሉት ኮሚሽኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በመሆን ሲመረምር ቆይቶ ተገቢውን ውሳኔ አስተላልፏል ብለዋል ፡፡
በውሳኔውም መሰረት፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ በሃላፊነት ላይ የነበሩት ግለሰቦችን ጨምሮ ሌሎች 14 የሚሆኑ የሀገረ ስብከቱ ሰራተኞች ከስራቸው እንዲታገዱ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፅህፈት ቤት ሀላፊ መምህር ይቅርባይ እነዳለ ቤተክርስቲያኗ ኮሚቴ በማቋቋም ጉዳዩን አጥንታለች ብለዋል፡፡
የሰባአዊ መብት ኮሚሽን ያሳለፈዉን የውሳኔ ሃሳብንም እንደምትቀበልና ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቅያ ከስራ የታገዱት እነዚህ አባቶች ደሞዛቸው ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ታስቦ እንዲከፈልና በማእረጋቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡