loading
‹‹የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ቃጠሎ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው›› አቶ ግርማ ቲመር የዱር እንሰሳ ጥበቃ ቦታዎች ልማት ዳይሬክተር

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ተከስቶ የደን የእሳት ቃጠሎ መነሻ ሆን ተብሎ በሰዎች አማካኝነት የተለቀቀ እሳት መሆኑን የዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን ለአርትስ ቲቪ አረጋገጠ።

‹‹የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ቃጠሎ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው›› ብለዋል አቶ ግርማ ቲመር የዱር እንሰሳ ጥበቃ ቦታዎች ልማት ዳይሬክተር ከአርትስ ቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

ከፓርኩን ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እና እስከአሁን ያለው የምርመራ ሂደት እሳቱ ሆን ተብሎ በሰዎች አማካኝነት የተለቀቀ እንደሆነ እንደሚያመላክት ነው ።

እንደዳይሬክተሩ ገለፃ የምርመራ ሂደቱ ወደዚህ መደምደሚያ ያመራው  ቃጠሎው በጀመረባቸው የፓርኩ ክፍሎች  ክብሪቶች መገኘታቸው እና ይህንኑ የሚመሰክሩ የአይን እማኞች በመገኘታቸው ነው፡፡

ከመጋቢት 19  ቀን 2011 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በፓርኩ ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ወደ 1 ሺህ 40 ሄክታር የሚሆነውን የፓርኩን ክፍል አቃጥሏል፡፡

በሃገራችን ለዚሁ የፓርኮች እና እንሰሳት ጥበቃ በደንብ የተቀናጀ ጥበቃ እና አስፈላጊ ቁሳቁስ  ባለመኖሩ የአካባቢው ማህበረሰብ እሳቱን ለማጥፋት በቻለው አቅም ሁሉ ርብርብ ሲያደርግ መክረሙ የሚታወስ ነው፡፡

በዚሁ ምክንያት  እሳቱን ለማስቆም በተደረገው ጥረት ውስጥ 5 ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አርትስ ለማወቅ ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በጠየቀው ድጋፍ ከእስራኤል በመጣ የእሳት አደጋ ተከላካይ ቡድን በሂሊኮፕተር በመታገዝ በተደረገው ጥረት  እሳቱን ማጥፋት መቻሉም ይታወሳል።

ከአፈሩ እሳት የዞ የመቆየት ባህሪ እና ከአካባቢው ሰፊ መሆን አንጻር ይህ ቃጠሎ ዳግም ላለማገርሸቱ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየተናገሩ ነው፡፡

ይህን ስጋት ለመቀነስ እና እንዲህ ያሉ የእሳት አደጋዎች ሲከሰቱ ሳይፋፋም ለመቆጣጠር ለማህበረሰቡ እና ለፓርኩ ጠባቂዎች ስልጠና የመስጠት ሂደት ላይ ስለመሆናቸው ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *