የሩዋንዳው ቡና በዓለም አቀፍ ሽልማቶች ተንበሸበሸ
አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በተካሄደው 3ኛው የኤርኔስቶ ኤሊ አለም አቀፍ የቡና ሽልማት ፕሮግራም ላይ ተሳትፎ “የምርጦች ምርጥ” እና “የቡና አፍቃሪዎች ምርጫ” የተባሉ ሽልማቶችን ጠራርጎ የወሰደው የሩዋንዳው ቡና ዓለም አቀፍ አድናቆትን አትርፏል።
ዘ ኢስት አፍሪካን እንደዘበው ይህ አለም አቀፍ ሽልማት ከተጀመረ ጀምሮ አንድ ቡና በሁለት ዘርፎች ሽልማቶችን ሲወስድ የሩዋንዳው ቡና የመጀመሪያ ነው።
ላለፉት ዓመታት ሩዋንዳ የዓለም ምርጥ የተባለውን ቡና በማብቀል፣ በማዘጋጀት እና ወደውጭ በመላክ የደቡብ አሜሪካን እና የምስራቅ እስያ ቡና አምራቾችን አስንቃለች ይላል ዘገባው።
ንጎሬሬሮ በተባለችው የሩዋንዳ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኝ ወረዳ ስም የተሰየመው የሩዋንዳ ቡና የውድድሩ ዳኞች በነበሩት ታዋቂ ዓለም አቀፍ ቡና ቀማሾች ምርጥ ተብሎ ተወስዷል።
ሩዋንዳ ለዓለም ዓቀፉ ገበያ ምርጥ የቡና ምርቶችን እያበረከተች ያለች ሃገር ብትሆንም ንጉሬሬሮ ቡና ግን የሃገሪቱ ምርጥ ቡና ነው ተብሎ ተመስክሮለታል።
የቡና መገኛ የሆነችው የምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2017 ለውጭ ገበያ ከላከቻቸው አስር ምርቶች ውስጥ ቡና ቀዳሚው ነው።
ከሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች ጋ ተደምሮ ያስገኘው ገቢ መጠንም 963 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።